Blog 8. Peace and Reconciliation by Dr. Getachew Haile (2015)

መጀመሪያ የመጀመሪያውን፤ ዕርቅና ሰላሙን

ጌታቸው ኃይሌ 

በዛሬው ጉባኤያችን ላይ በአካል ለመገኘት ብችል ምንኛ በተደሰትኩ ነበር። ብገኝ ኖሮ የማቀርበውን ሐሳብ በሩቁ ሆኜ በጽሑፍ እንዳቀርብ ከተፈቀደልኝ፥ ከአሁን በፊት በስብስቦችና በብትን ያቀረብኩትን እንዳዲስ ላቅርብ።

የኢትዮጵያዊነት ማኅበራችን ተልእኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኑሮው በአንድነት አይቶ በአንድነት የፈታው ሕልም እንዲደርስ ማድረግ ነው። ሕልሙ በነፃነትና በሰላም እየበለጸጉ መኖር ሲሆን፥ ከታየና ከተፈታ ብዙ ትውልዶች አልፈዋል። ግን አልደረሰም። ለምን አልደረሰም ብለን ብንጠይቅ፥ ሁላችንም የምንስማማበት መልስ ያለ አይመስለኝም። መንፈሳዊ ሕልም እና ሥጋዊ ሕልም የተለያዩ ናቸው። መንፈሳዊ ሕልም ከላይ ኀይል ይላካል፤ እንደ ዮሴፍ ስጦታ ያለው ሕልም ፈቺ ይፈታዋል፤ ተስፈኛው ቁጭ ብሎ ሕልሙ እስኪፈጸም ይጠብቃል። ጊዜውን ጠብቆ ሕልሙን በላከው ኀይል ይፈጸማል።

ሥጋዊ ሕልም ግን ከነትርጒሙ ከሰው አእምሮ ይፈልቅና በሰው ኀይል ከሥራ ላይ ይውላል፤ ይደርሳል፤ ይፈጸማል። እንዲህ ከሆነ፥ ጥያቄው መሆን ያለበት፥ “ሕልሙ ታልሞ ከተፈታ ብዙ ጊዜ ከሆነው፥ ገና ከሥራ ላይ ያልዋለው ለምንድን ነው? ከሥራ ላይ የሚያውል የሰው ኀይል ጠፍቶ ነው ወይስ ዘዴው አልገለጽላችሁ ብሎን ነው?” የሚል ነው። መልሱ ሁለተኛው ይመስለኛል። የሰው ኀይል አለ፤ ሕልሙ ከታለመና ከተፈታ ጀምሮ ሕልሙን በሥራ ላይ የሚያውሉ ኀይላት ተነሥተው ተፋልመዋል። ትግሉ በተለይ የተፋፋመው ከተማሪዎቹ ንቅናቄ ጀምሮ ቢመስልም፥ የተጀመረው በብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ ነው። አሁንም በሰልፍ ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት እንኳን፥ በትጥቅ፥ በዜና ማሰራጫ ፥ በጽሑፍ፥ በፖርቲ እንደሚካሄድ እናውቃለን። ትግሉ ውጤታማ ካልሆነ፥ አመርቂው ዘዴ ቢጠፋን ነው። 

የታሰበውና የተሞከረው በጥንቱ ሥርዓት የተቋቋመውን መንግሥት አፍርሶ በአዲስ ሥርዓት ለመገንባት ነበር። ግን አንደኛ፥ የጥንቱ ሥርዓት ገጽታው አንድ ዓይነት መሆኑ (ንጉሣዊ አስተዳደር መሆኑ) የአዲሱ ሥርዓት ገጽታ ብዙ (ሕገ መንግሥታዊ የንጉሥ አስተዳደር፥ ዲሚክራሲያዊ ሊበራል ወይም ኅብረሰባዊ ሪፐብሊክ) ሊሆን እንደሚችል፥ ሁለተኛ፥ ጎሳዎች የየራሳቸውን መንግሥት የማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸው እንዳንገነዘብ አድርጎናል። ስለዚህ፥ በፈረሰው ቤት ምትክ ሁል-አቀፍ አዳራሽ የመሥራት እርምጃ ልንወስድ አልቻልንም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ምኞት ጎሰኞች አጨናገፉት።

ትግላችን ይቀጥላል። ግን መጀመሪያ የእስከ ዛሬው ትግል ለምን ውጤታማ አልሆነም? ብለን መጠየቅ አለብን። ለትግል ጕዞ የጀመርነው መንገድ የት የሚያደርስ ነው? ልንደርስበት የምንፈልገው አገር ስሙ ማን እንደሆነ ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት ማረጋገጥ አለብን።

የእስከ ዛሬው ትግል ብዙ ሰማዕታት አፍርቶ ሳለ፥ ውጤታማ ያልሆነበት ምክንያቶቹ ብዙ ሊሆኑ
ይችላሉ። አንዱን ምክንያት እንደመሰለኝ ገምቼ፥ የመሰለኝን መፍትሔ “በኢትዮጵያ ሰላም የሚያመጣ የአማራ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ያስፈልጋል” በሚል ርእስ በቅርብ ጊዜ ለሕዝብ አቅርቤ ነበረ። በዛሬው ጽሑፌ የማቀርበው ትችት ከዚያኛው ጽሑፍ ይዞታ አንዱን ክፍል ገንጥሎ የሚከልስ ይሆናል። በፊት ያቀረብኩት ጽሑፍ የሚለውና አሁን እንደገና ላብራራው የምፈልገው፥ የትግሉ ዘመቻ የተካሄደው
የተለያየ ዓላማ ባላቸውና በማይግባቡ፥ እንዲያውም በተካሰሱ ሠራዊቶች ነበር፤ አሁንም ነው የሚል አስተታየት ነው። ከሳሾች “አፈ ጎሳ” ነን የሚሉ በጎሳ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ያቋቋሙ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ተከሳሾሹ አሁን ግልጽ እንደሆነልኝ፥ ኢትዮጵያዊነትን አጥብቀው የያዙት
ናቸው። ከሳሾቹ ተከሳሾቹን አማርኛ ስለሚናገሩ “አማሮች” ይሏቸዋል። የክሱ ጭብጥ፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ጎሳዎች ተበድለዋል፥ ተጨቁነዋል፥ አንዳንዶቹም ተሽጠዋል። ይኸንን ሁሉ ወንጀል የፈጸመው የአማራ ሕዝብ ነው፤ የሚል ነው።

እነዚህ ከሳሾች ወደኋላ እየሄዱ እሮሮና ዋይታ፥ ቁጭትና በቀል፥ ቀለል ሲል ደግሞ ስድብ ያሰማሉ። መፍትሔያቸው አማራን ማሳደድ፥ መግደል፥ ንብረቱን መዝረፍ፥ ከዚያም አልፈው “የሰፈርንበትን መሬት ይዘን ከኢትዮጵያ እንለያለን” የሚል ነው። “የበደሉ ዓይነት ይለያይ ይሆናል እንጂ ያልተበደለ የለም” እያሉ ብዙዎች ቢያስታውሱም፥ ቁጭቱና ቁጣው አልበረደም። በአንድ በኩል፥ “እኛ በተለይ ተበድለናል” የሚሉና በሌላው በኩል፥ “የተበደልነው ሁላችንም ነን” የሚሉ ወገኖች ድምፃቸውን በየቤታቸው ሆነው ያሰማሉ፥ ይወነጃጀላሉ እንጂ፥ ለመግባባት፥ ያም ካልሆነ ለመሰማማት፥ ተቀራርበው የተነጋገሩበት ጊዜ መኖሩ ትዝ አይለኝም። ላቀርብ የምፈልገው ሐሳብ ተቀራርበን እንወያይ የሚል ነው። ልዩ በደል ደርሶብናል የሚሉ ወገኖችን ከሁሉም የባሰ የሚያስቆጣቸው፥ “ይህ ችግር መጀመሪያ የተማሪዎቹ ንቅናቄ፥ አሁን ደግም ወያኔዎች የፈጠሩት ችግር እንጂ፥ ሁላችንም በሰላምና በእኩልነት አብረን የኖርን ሕዝብ ነን” የሚል ሐሳብ ሲሰነዘር ነው። በነሱ እምነት፥ በደሉን ተማሪዎቹና ወያኔዎች አጎሉት እንጂ፥ መኖርስ አብሮን የኖረ ነው። ልዩነቱ እኛን የሚሰማንን ያህል አማራው ወይም በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ሕዝብ አይሰማቸውም ነበር ይላሉ።

በዚህ ነገር ላይ ከሳሾችም ተከሳሾችም እውነት አላቸው። ለአንዳፍታም ቢሆን የከሳሾቹ ጠበቃ ልሁንና፥ ከተማሪዎቹ ንቅናቄ በፊት የጎሳዎች ማጕረምረም እንደነበረ መካድ እንደማይቻል፥ ለማሳየት ያህል፥ አንዳንድ ድርጊቶችን ከታሪክ ሰነድ ውስጥ እናስታውስ፤

ትውስት አንድ፤ ከኢትዮጵያው አፄ (ማለት ከንጉሠ ነገሥቱ) ሥር ንኡሳን ነገሥታት እንደነበሩ እናስታውሳለን። ከነዚህ አንዳንዶቹ የእስላም ነገሥታት ነበሩ። ከ1426 እስከ 1460 የነገሠው አፄ ዘርአ ያዕቆብ የኢማም በድላይን ወረራ ለመመከት ዘመቻ ሲያውጅ፥ በሥሩ ካሉት ነገሥታት አንዱ የእስላሞች ንጉሥ ለእርዳታ ልምጣልህ ብሎ ቢልክበት፥ “ግዴለም ካለህበት አትነቃነቅ” ብሎ መለሰለት። ታሪክ ጸሐፊው ምክንያቱን እንደመዘገበው፥ አፄ ዘርአ ያዕቆብ እርዳታ ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን፥ ከኢማም በድላይ ጋር ሲዋጋ የእስላሙ ንጉሥ ለእርዳታ የመጣ መስሎ ከኋላው እንዳይመታው ፈርቶት ነው። አንድ የሀገር መሪ ከሀገር ጠላት ጋር ሲዋጋ እንዴት የሀገሩን ሰው ከድቶ ከጠላት ጋር ይወግናል ብሎ ይፈራል? ከመዝመታችን በፊት መጀመሪያ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት አለብን።

ትውስት ሁለት፤ ከኢማም በድላይ ቀጥሎ በኢትዮጵያው አፄ ላይ ያመፀው ኢማም አሕመድ ግራኝ ነበር። በዚያን ጊዜ ፈላሻ የሚባሉት ቅማንቶች ለወራሪው ለኢማም አሕመድ ግራኝ እርዳታ እንደሰጡት ተመዝግቧል። አንድ የሀገር መሪ ከአማፂ ጋር ሲዋጋ እንዴት የሀገር ሰው መሪውን ይከዳል? የጋራ ሀገር ጠላትን ለማስወገድ የትግል ክተት ከማወጃችን በፊት መጀመሪያ ይኸን ዓይነት መሰናክል ትግላችንን እንዳያሰናክልብን አሁኑኑ አስፈላጊውን መፍትሔ መፈለግ አለብን።

ትውስት ሦስት፤ በጻድቁ ዮሐንስ ዘመን (1660-1674) የኖሩ አባ አካለ ክርስቶስ የሚባሉ አንድ መነኩሴ ነበሩ፤ ገድላቸውን ሳነብ በውስጡ በግዕዝ የተመዘገበውን ወደአማርኛ ተርጕሜ ከዚህ በታች የጻፍኩትን አገኘሁ፤

በዚያን ዘመን አራ ደንጐራ ከምትባል ሀገር የሚኖሩ ወታደሮች ነበሩ። ማተባቸውን ከአንገታቸው ላይ ፈትተው በየ ጦራቸው ላይ ሰቅለው ወደ ብፁዓዊ አቡነ አካለ ክርስቶስ መጡና እንዲህ አሉት፤ “አባት ሆይ፥ ዱሮ አረማውያን ስለነበርን ሕዝበ ክርስቲያኑን እንበቀላቸው፥ ቤተ ክርስቲያን እናቃጥል ነበር። ዛሬ ግን በእግዚአብሔር ምሕረት መንፈሳዊት ጥምቀትን አግኝተን፥ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተደባልቀናል። በክርስቲያን
ሕግም ከእነሱ ጋር አንድ ሆነናል። ቤተ ክርስቲያንን ወደናታል። በማቃጠል ፈንታ ወደሷ ሄደን ልንገነባት ድንጋይ፥ እንጨት ውኻ በመሸከም ደክመናል። ከዚህ ሁሉ በኋላ፥ እነሆ እንደኛው ያሉት ጓደኞቻችን ወታደሮች ከሀገራችን በኃይል ያባርሩናል። ወደቀድሞው ባህላችን እንድንመለስም ያስገድዱናል። በጸሎትህ አትርሳን። ከተቻለህም ከእጃቸው አውጣን።

አዲስ ክርስቲያኖች ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር መዋሐድን በአክብሮት ሲፈልጉ፥ መበረታታት ሲገባቸው፥ የመንግሥት ወታደሮች መሬታቸውን ከቀሟቸው፥ በአረመኔነታቸው ጊዜማ ግንኙነታቸው ምን ይመስል ነበር ?

ትውስት አራት፤ የሀገር ጠላት ሲነሣ፥ ሕዝቡ እንደሚተባበር በማስረጃነት የሚጠቀሰው የአፄ ምኒልክ አመራርና የ1888 ዓ.ም. የአድዋ ድል ነው። ማስረጃነቱ የማይካድ ነው፤ ብዙዎች ተባብረውበታል። ሆኖም ሁኔታው በሚገባ አልተመረመረም። ለምሳሌ፥ አፄ ዘርአ ያዕቆብ የፈራውን አፄ ምኒልክም ፈርተውት ነበር። ታሪኩን ታሪክ ጸሐፊያቸው ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ እንዲህ ሲሉ መዝግበውታል፤

አጼ ምኒልክ ግን ወደ ትግሬ [ወደ አድዋ] ሊዘምቱ ካዲስ አበባ ተነሥተው አምባሰል ሲደርሱ (የመሐመድ አንፋሪ ቱርክ ባሻ አብደርሁማን ክፋት ማሰቡን) በሰሙ ጊዜ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋራ ወደትግሬ ሊዘምቱ የነበሩትን መኳንንት ራስ ወልደ ጊዮርጊስንና ደጃዝማች ተሰማን (ከግዛት) አገራቸው መራቅ የተነሣ ወደኋላ ቀርተው ነበርና ወደ አውሳ እንዲዘምቱ እንዲህ ብለው ላኩባቸው።  

“ከኔ ጋር ያለው ሠራዊት ብዙ ነው ልክና መጠን የለውም። እግዚአብሔር ካልተለየን በትግሬ በኩል ላለው ጦር ይበቃል። እናንተም ወደ አውሳ ዝመቱ” ብለው አዝዟቸው። . . . እነዚህም ሁለት መኳንንቶች ታንኮበር ወህኒ አዛዥ ወልደ ጻድቅን ጨምረው በታዘዙት ወደ አውሳ ዘመቱ።

የዘመኑ መፍትሔ ያመፀን እንደዚህ ማስገበር እንጂ ማባበልና ማሳመን፥ ብሶቱን መስማትና መፍትሔ መፈለግ አልነበረም፤ ግን እስከመቸ ለጠላት ስንመች እንኖራለን?

(ታሪኩን ለማሟላት ያህል፥ አፄ ዮሐንስም ወደ ጉራሌ በዘመቱ ጊዜ፥ አውሳን እንውጋ ብለው ነበር። ግን አውሳ በዚያን ጊዜ ለሸዋ ንጉሥ ይገብር ስለነበረ፥ ታሪክ እንደሚነግረን፥ “አጼ ምኒልክ ካያቴ ከቅድም አያቴ እስከኔ ድረስ ከፈቃዴ ወጥቶ የማያውቅ ዜጋዬ ነው ብለው አገሩን ከጥፋት አዳኑት። እስከዚህ ቀን ድረስ ካጼ ምኒልክ ፈቃድ አልወጣም ነበር። ኋላ ግን አብድርሁማን የሚባል የተጐሬ አዳል” ከጣሊያኑ ከአንቶኔሊ ጋር ተስማምቶ ሱልጣን መሐመድ አንፋሪን አስከዳ።)

ትውስት አምስት፤ ሁለተኛው የኢጣልያ ወረራና የማይጨው ጦርነት ታሪክ (1928 ዓ.ም.) የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህ ጦርነት ጊዜ ራያዎች እንደከዱ ተመዝግቧል።) የነሱ ክዳት ለድል ማጣታችን ምክንያት ባይሆንም፥ በዘማቹ ላይ የማይረሳ ጉዳት አድርሷል። “ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንዲሉ፥ ንጉሠ ነገሥቱ በጦርነቱ ላይ እያሉ የራያ መሪዎችን አስጠርተው ከፋሺስት ወራሪዎች ጋር እንዳይሰለፉና አገራቸውን እንዳይበድሉ አባብለዋቸውም ነበር፤ አልሰሙም። የራስ ወገን ከኋላ እንዳይወጋ እስከ መቸ ሲገላመጡ መኖር ይቻላል?

ትውስት ስድስት፤ ከማይጨው ሽንፈት በኋላ፥ አርበኞች ጥቁር አንበሳ በሚል ስም ተደራጅተው፥ በደቡብ ኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል አካሂደው ነበር። አገሬው ድጋፍ በመስጠትና በማበረታታት ፈንታ፥ ከጠላት ጋር ወግኖ ይወጋቸው ነበር። ደቡቡ አዲስ አበባ ላይ ለሰፈረው ጠላት ሩቅ ሆኖ ሳለ፥ አርበኞቹ በዚህ ምክንያት ትግላቸውን ጥቂት ጊዜ እንኳን መቀጠል አልቻሉም። በተቃራኒው በጎጃም እነበላይ ዘለቀና በሸዋ እነአበበ አረጋይ ግን ጠላትን በቅርቡ ሆነው እስከመጨረሻው ድረስ አስጨንቀው ይዘውት ነበር። የሁለቱ ሁኔታ መለያየት ለምን እንደሆነ ሳይሸፋፈን ተጠንቶ መፍትሔ አልተፈለገለትም። 

 ወያኔዎች ኢትዮጵያን ድል የነሡትና እስካሁን ድረስ በወራሪነት ተንፈራጠው በሥልጣን ዙፋን ላይ የተቀመጡት፥ በዚያው ከነሱ በፊት የተነሡ ጠላቶቿ በተጠቀሙበት የጎሳዎች ቅሬታ በመጠቀም ነው። “ከአማራ ጭቆና አድነናችኋል” ለማለትና “አማራ ተመልሶ መጥቶ እንዳይጨቁናችሁ ከእኛ ከባለውሎታዎቻችሁ ጋር ቁሙ” ብሎ ለማሳመኛ ያህል፥ ለጎሳዎች ከሚመኙት ቆንጠር አድርገው ሰጥተዋቸል። ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል እንዲሉ፥ ለትልቁ ዓላማ፥ ማለትም በነፃነት ለዲሞክራሲያዊ ኑሮ ከዲሞክራቶች ጋር አብረው ለመታገል አላሰቡበትም። ወያኔ የሰጣቸውን የሚያስተያዩት ካለፈው ጋር እንጂ፥ ዲሞክራሲ ሲሰፍን ከሚያገኙት ሙሉ ነፃነት ጋር አይደለም። ባጭሩ፥ “ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል” የሚለው ፍልስፍና የአእምሮ እስረኞች ሆነዋል። ማስፈታት ግዴታችን ነው።

ወያኔዎች ከጎሳ ድርጅቶች የሚፈልጉት ድጋፍ በአማራ ስም ኢትዮጵያዊነትን ለማጥቃት ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ በማንም እጅ መጠቃት የለበትም። ሆኖም የኛ ቁጣ ያተኮረው ከአማራው መገደል አልፎ፥ እንዲገደል ከተወሰነበት ምክንያት ላይ ነው። ወያኔዎች ለጎሰኞቹ የሚሰጡት ምክንያት፥ አማራ ስለበደላችሁ ምቱት ነው። እውነትም እነ ጃራ፥ “እድሜ ይኸንን ዕድል ለሰጠን ለወያኔ” እያሉ ብዙ አማራ የሚሏቸውን አርደዋል። ወያኔዎች ሊደብቁት ያልቻሉት በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑትን ለመምታት የገፋፋቸው ድብቅና ሩቅ ዓላማ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍለው፥ አገሪቱን እንደፈለጉ እንዳይጫወቱባት በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ሕዝብ ስለሚያስቸግራቸው ነው። ስለዚህ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በቀጥታና በእጅ አዙር መምታት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል።

በኢትዮጵያዊነት የሚያምነውና አማርኛ የሚናገረው ሕዝብ ቍጥር ለጊዜው ቀላል አይደለም። እንዲያውም ከአደጋ ላይ የጣለው ብዛቱና እምነቱ ነው። ጎሳዎችን በኢትዮጵያዊነት በሚያምነው ላይ ማስነሣት ሕዝብ ማጫረስ ነው። በኢትዮጵያዊነት በሚያምነው ሕዝብ ለመቆጣት ሁለት ምክንያት አለው፤ አንደኛው፥ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ሲሆን፥ ሁለተኛው በአባቶቻቸው ፊታውራሪነት የተገነባች ኢትዮጵያ መጎሳቆሏን አለመቀበል ነው። የምንሰማው እውነት ከሆነ፥ ወያኔዎች የዘመቱት በተወለዱት ላይ ብቻ ሳይሆን ባልተወለዱትም ላይ ነው።

አንድ ሕዝብ እርስ በርሱ ተፋጦና ተጣልቶ አብሮ በሰላም መኖር፥ በሀገር ጠላት ላይም አብሮ መዝመት አይቻልም። ካሁን በፊት ተችሎ እንደሆነ፥ ለዛሬው ችግራችን አርአያ አልሆነንም። ወያኔዎች ጠላቶች እንጂ፥ የጋራ ዓላማ ጠላቶች መሆናቸውን ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት አልቻልንም። የሕዝብ ጠላት መሆናቸውን እምናውቅ እንኳን የየግል ድርጅት ጠላት እንጂ የጋራ ጠላት አላደረግናቸውም። ለምሳሌ፥ አንዱ ወገን ጠላት የሚያደርጋቸው፥ በዐወጁት ሕገ መንግሥት ውስጥ ለጎሳዎች የመገንጠል መብት የሚሰጠውን አንቀጽ 39ን ማወጃቸው ሲሆን፥ ሌላው ወገን ደግሞ ይህ ራሳቸው ያወጁት አንቀጽ የሰጠውን የመገንጠል መብት መንፈጋቸው ነው። ታዲያ ምን ይሻላል? የገራ ጠላት ለጋራ መብት መታገልን አይወልድም። ወያኔዎች አንቀጽ39ን ያወጁት የጎሳዎችን ውገና ከተቃዋሚው ዘንድ ቀምተው ለመውሰድ መሆኑን አንርሳ። የሀገር ጠላት የማንም ወዳጅ ሊሆን እንደማይችል አስረድተን የተወሰደብንን የጎሳዎችን ወገንነት ማስመለስ አለብን።

ይኸንን ችግር ሳንፈታ በጋራ ጠላት ላይ አብሮ መዝመት አይቻልም። የሚያዋጣው ከመዝመታችን አስቀድመን መጀመሪያ በአንዳች ዘዴ ሕዝባዊ ዕርቅ ማውረድ ነው። ስንታረቅ ወያኔዎች በአንቀጽ 39 ደልለው የወሰዱብንን ውገና እናስመልሳለን። የአንቀጽ 39 ምንጩ አለመታረቅ ነው። እርግጥ ሳንታረቅ እንቀር ይሆናል። ሆኖም፥ ብዙ ጎሳዎች ያሉባቸው ሀገሮች (ለምሳሌ ህንድ) ዲሞክራሲን አስፍነዋል። ጥንታዊት ኢትዮጵያም ጎሰኝነት-አልባ የዲሞክራሲ ሥርዓት ልታካሂድ እንደምትችል አምናለሁ።

የምሁራኑ የምስክርነት ጥናቶች መጽሐፍ ሆነው ይታተማሉ። ለመጽሐፉ “መርዶ ለወያኔ” የሚል ስም እናወጣለን።

ልደጋግመውና፥ የትግል መጀመሪያው ዕርቅ ነው። ዕርቅ ከሌለ ከሳሹም ተከሳሹም የወያኔ ሰለባ ሆነው ይቀራሉ። ዕርቅ ከሌለ አብሮ መዝመት እንደማይቻል እየታየ ነው።

የጋራ ግብና የጋራ ዓላማ፤

ዕርቅ ወርዶ ጠላትን የጋራ ከማድረግ ላይ ከተደረሰ፥ የሚቀጥለው ግዴታችን ከጋራ ግብ መድረስ ነው። ጠላትን የጋራ ማድረግ ብቻውን የጋራ ግብ አያስገኝም። የታረቁት ወገኖችን የጋራ ግብ የሚቀይስና ሕገ መንግሥት የሚያረቅ ኮሚቴ ማቋቋም ይኖርባቸዋል። ዕርቅ ሳይኖር፥ ስለ መንግሥት ዓይነት፥ ስለ ሕገ መንግሥት መነጋገር ነዋሪ የማይፈልገው ቤት እንደመሥራት ይቈጠራል። ኮሚቴው ጥናቱን ሲጨርስ ከምሁራኑ የምስክር ወረቀቶች ጋራ አብሮ ይታተማል። ታጋዮች ቃል እንዲገቡ የምፈልገው፥ እድሜው ፓርቲዎች ለውድድር ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ ብቻ የሚቆይ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲያቋቁሙ ነው። ያለፉት የብጥብጥ ዘመናት ለሕዝቡ የፖለቲካ ንቃት ስለሰጡት፥ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለማቋቋም ከአንድ ዓመት የበለጠ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው አይመስለኝም።

ድርጅታችን ሐሳቤን ተቀብሎ በሥራ ላይ እንደሚያውለው ተስፋ አደርጋለሁ። ጉባኤውን እኔው
ልጠራው ብችል ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፤ ግን በአንድ ሰው ብርታት የሚፈጸም አይደለም። ባይሆን ግብረ ኀይሉ ተቋቁሞ ዝርዝሩን እንዳወጣልን፥ ጉባኤውን ለማካሄጃ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እማፈላለጉ ላይ እተባበራለሁ። ለሰላም ጉዳይ ዓለም-አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የእርዳታ እጃቸውን ይዘረጉ ይመስለኛል። 

ለሕዝባዊ ዕርቅ የሚሆን ዘዴ፤

ሐሳቤ፡ ተቀባይነት ካገኘ፥ እንድንሞክረው የማቀርበው ዘዴ አንድ የዕርቅንና የሰላምን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ግብረ-ኃይል ማቋቋም ነው። ግብረ-ኃይሉ እንዲያከናውን የምፈልገው፥ የሀገር ጠላት ሁላችንንም የሚያቆረቍዝ ስለሆነ፥ አብረን እንድንዘምትበት፥ በማህላችን ያለውን አለመግባብት ጥቂት ቀናት በሚወስድ ጉባኤ እንድንወያይበት ነው። በጉባኤው ላይ ከሳሾችና ተከሳቾች ለምስክርነት በሚጠሯቸው ምሁራን አማካይነት ጉዳዩ ይሰማል። የከሳሽ የምሁራን ምስክሮች ጥናት ላይ የተመሠረተ የክስ ጽሑፍ ያቀርባሉ፤ የተከሳሽ የምሁራን ምስክሮች በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ሕዝብ እንዳልበደለ የራሳቸውን ጥናት ያቀርባሉ። ቀን ቀን ስንወያይ እንውላለን፥ ማታ ማታ የተለያዩ ሀገራዊ ትርኢቶችና ፊልሞች እናያለን። ግጥሞች ይነበባሉ፤ ቀረርቱ ይሰማል። የከሳሽና የተከሳሽ ወገኖች አብረው ለመጫወትና ለመወቃቀስ ዕድል ያገኛሉ። 

 

Tesfamichael MakonnenComment